christmas star Mahbere Abune Selama- self help association, support those in need, Spiritual gatherings, youth and adult counselling  christmas star

lo 1

                             cross animation smallክርስቲያንና ስነ - ምግባሩcross animation small

እስራኤል ከግብጽ ምድር ከባርነት ቀንበር ነጻ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ ሳሉ ማጉረምረማቸውና ፈጣሪያቸውን ማስቆጣታቸው የታወቀ ነው፡፡  በዚህም ምክንያት በሙሴ በኩል ሕዝቡ የሚመሩበት ፈቃደ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ሕግ በደብረ ሲና ተራራ ተሰራ፡፡ ሙሴም ሕዝቡ ፈጣሪያቸውን የሚያመልኩበት ከኃጢአት ርቀው የሚጠብቁትን ሕገ ኦሪት ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብሎ ለሕዝቡ አውጆአል፡፡ ሕዝቡም ይህም አምላካዊ ሕግ ተቀብሎ ሲጠብቀውና ሲመራበት መኖሩ ግልጽ ነው፡፡  ይሁን እንጂ አመጸኞች ሲቀጡበት ሕግ ፈጻሚዎች ሲመኩበት ሲመሰገኑበትና ከአምላካቸው ዘንድ በረከትን ሲቀበሉበት ኖረዋል፡፡  ይህም ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዘመነ ወንጌል ደርሷል፡፡ 

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሕግ ፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን ለሙሴ የተሰጡትን አስሩን ትእዛዛት በስድስቱ ቃላተ ወንጌል የረዘመውን በማሳጠር የላላውን በማጥበቅ በማሳጠርና በመጠቅለል ለተከታዮቹ አስተምሯቸዋል፡፡  በዚህም ሕጉም ፍጹም ሊሆን ችሏል፡፡  ለተከታዮቹም ከወደዳችሁኝ ሕጌን ጠብቁ በማለት አዝዞአቸዋል፡፡  በዚህ መልኩ የሱ ተከታይ የሆነ ሁሉ ይህን ሕግ መጠበቅ ይገባዋል፡፡  እንግዲህ ማመን ከመረዳት የተነሳ ነው፡፡  መረዳትም ከመማርና ከማንበብ የተነሳ ነው፡፡  እንደተባለው ቅዱሳት መጻሕፍትን ለማንበብና ለመማር አመቺ ይሆንልን ዘንድ ይህን ክርስቲያናዊ ስነምግባር የሆነውን አምላካዊ ሕግ የሆነውን አስርቱ ቃላትንና ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን አስሩ አንቀጸ ብጹአንን እንዲሁም አንቀጸ ምጽዋትን አንቀጸ ጸሎትንና አንቀጸ ጾምን በቅደም ተከተሉ መሰረት እንማረዋለን፡፡  ይህ ቃል ለጊዜው ለተወሰኑ ሰዎች ቢሰጥም ፍጻሜው ግን በአለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች ነው፡፡  ይህም ክርስቲያናዊ ስነምግባር በሦስት ክልሎች ይከፈላል፡፡

አንደኛው ክፍል አስርቱ ቃላት ወይም ኦሪታዊ ሕግ የሚባለው ነው፡፡ 

ሁለተኛው ክፍል ስድስቱ ቃላተ ወንጌል /ሐዲስ ሕግ/ የሚባለው ሲሆን

ሦስተኛው ክፍል አንቀጸ ብጹአን በመባል ይታወቃሉ፡፡

አንደኛ ክፍል ክርስቲያናዊ ስነምግባር በሁለት ክፍል ይከፈላል፡፡  ከአንድ እስከ ሦስት ያሉት አንቀጾች የአምላክን ሕልውና ቅዱስነት ክቡርነት እንዲሁም አምልኮታችንን ተገዢነታችንን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናሳይባቸው መንገዶች ሲሆኑ የቀሩት ስድስቱ አንቀጾች ግን ማንኛውም ሰው ለሁሉም የሰው ልጅ ሴት ወንድ ትልቅ ትንሽ ሳይል የሚያደርገውና የሚፈጽመው ሕግ ነው፡፡  እነዚህም አንቀጾች ሰው ከሰው አብሮ የመኖርን ዘዴ የሚያስተምሩ ሰላምና ፍቅር አንድ እምነት መተሳሰብ የሚገኝባቸው የሰው ልጅ ሁሉ ተባብሮ ሊጠብቃቸውና ሊፈጽማቸው የሚገባው መሆኑን የሚገልጹ ናቸው፡፡  ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕገ መንግስት አውቀን ኑሮአችን የሰላምና የጤና የፍቅር ኑሮ ይሆንልን ዘንድ ቃሉን ማጥናትና በቃሉ መኖር በተማርነው ትምህርት መጽናትና መመላለስ ይኖርብናል፡፡  እግዚአብሔር ዓይነ ልቦናችንን ይክፈትልን አይነ ልቦናችንንም ያብራልን አሜን፡፡

ከእኔ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ

በእግዚአብሔር ሕገመንግስት እና በክርስቲያናዊ ስነምግባር ትምህርታችን በመጀመሪያው አንቀጽ የምንማረው ስለ አምልኮተ እግዚአብሔር ይሆናል፡፡  ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ በላይ በሰማይ በዚህም በምድር እንደሌለ እንረዳለን እሱ እራሱ እግዚአብሔር ዘላለማዊና በማይሻረው ቃሉ ተናግሯል፡፡  እግዚአብሔር አምላክ ይህን የአምልኮት ስርአት የሰጠው ለአብርሃም ዘሮች ለእስራኤል ነው፡፡  እስራኤልን ከግብጽ ምድር በብዙ ድንቅ የተአምር ስራ ከባርነት ቀንበር ነጻ ካወጣቸው በኋላ የሚሄዱበት አገር በተለያየ የጣኦት አምልኮ የረከሰና የተበከለ ስለሆነ በዚህ አይነቱ አምልኮ እንዳይረክሱና እንዳይበከሉ አስቀድሞ ይህን የአምልኮ ስርአት ሰራላቸው በቀድሞ ግዜ እንደዛሬው ሁሉ የኃጢአት አይነቱ ስራውም ሳይበዛ ዋናው ኃጢአት አመልኮ ባእድና እውነተኛውን አምላክ ቸል ማለት ነበር፡፡ 

በሌላ ባእድ አምልኮ ጣኦት እንዳይሰናከሉ ከፍተኛ መመሪያ ሰጣቸው ነገር ግን እስራኤል እውነቱን በሐሰት አምላክነቱን በጣኦት በመለወጥ አሳዘኑት ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ነኝ ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጠ ዛሬም ቢሆን ይህን ትእዛዝ የማይፈጽሙትን ሕጉን የዘነጉትን ሰዎች እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ከእኔ ሌላ ባእድ አምላክ አታምልኩ ወደ እኔ ተመለሱ ይላቸዋል እግዚአብሔር አምላክ በሌላ አጉልና ከንቱ ልማድ እንዳይጠመዱ አስቀድሞ ይህን የመሰለ ሕግ ከሰጣቸው በኋላ አታምልኩ ያላቸውን ጣኦት አመለኩ አታድርጉ ያላቸውን ምስል በፊታቸው አደረጉ በዚህ ምክንያት ቀጣቸው፡፡  እንግዲህ እኛም ክርስቶስ ከኃጢአት ቀንበር ነጻ ካወጣን በኋላ በደሙም ካጠበና ከቀደሰን በኋላ እንደገና ተመልሰን የኃጢአት ተገዢዎች ብንሆን እንደ እብራውያን መሆናችን እስራኤልንም መምሰላችን ነው፡፡  ዘጸ 321-8፡፡  ምክንያቱም አንዱን ልባችንን ለሁለት ከፍለን በሁለት ልብ እግዚአብሔርን ማምለክ እና እንደ እግዚአብሔርነቱ ልናመሰግነው አንችልምና ዘጸ 3412-15፡፡  ከአንድ ምንጭ መራራና ጣፋጭ ሊቀዳ አይችልም፡፡ ዘጸ 2313 ያዕ 311፡፡  ስለዚህ በእኛም ልብ ውስጥ አምልኮተ ባእድና አምልኮተ እግዚአብሔር መቀረጽ የለበትም እግዚአብሔር እንዲህ አይነቱን አምልኮ አይቀበለውምና፡፡  1 ቆሮ 1021-22፡፡

እንግዲህ የእግዚአብሔርን ክብር ምስጋና ውዳሴ እንወቅ እንረዳ እንደ እግዚአብሔርነቱም ልናመሰግነው ልናከብረው ልናወድሰው ከፍ ከፍ ልናደርገው ውለታውን ልናስታውስ ይገባናል፡፡

ማር 1230 እውነተኛ አምልኮተ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው በፍጹም ሐሳባቸው መውደድ ነው፡፡  ማቴ 721 ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግባት የምንችለው ፍቃዱን ስንፈጽም ነው፡፡  ዮሐ 422-24 እውነተኛ አምልኮ በልብ ዝንባሌ እንጂ በቦታ አይወሰንም፡፡  ዘጸ 2319 የተመረጠውን መልካም የሆነውን ለአምላክ መስጠት ከሱ ተገኝቷልና፡፡  ዘጸ 1910-11 የምናመልከው ሁሉ በአካልም በኑሮም ንጹሕ ሕልውና ሊኖረን ይገባል፡፡

ቀናተኛ አምላክ ነው ሕዝ 83-18 በቤተመቅደስ ውስጥ የቆመውን ጣኦት ለሕዝቅኤል እግዚአብሔርን አሳየው፡፡  2 ዜና 331-17 ምናሴ ሰሎሞን በሰራው ቤተመቅደስ ውስጥ ጣኦት በማቆሙ እግዚአብሔርን አስቀና፡፡  መዝ 7755-64 የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን አስቆጡት እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፡፡  1 ነገ 1821 እስከመቼ ድረስ በሁለት ሐሳብ ታነክሳላችሁ፡፡

የምታመልኩትን ምረጡ ኢያ 2415

1 ነገሥት 1910-14 ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ ቃልኪዳንህን ትተዋልና 14 ቁ፡፡

የአምላክህን ስም ከንቱ አታድርገው ዘጸ 207

ስመ ማለት ግብርን ጸባይን ሁኔን የሚገልጽና የሚያንጸባርቅ ነው፡፡  የእግዚአብሔር ስም ይህንኑ ነው የሚያስረዳው፡፡  ስለዚህ ቅዱስና ክቡር ከስም በላይ የሆነውን ስሙን በከንቱ እንዳንጠራ በክርስቲያናዊ ስነምግባር ትምህርታችን አምላካዊ ሕግ ያስተምረናል፡፡  አንደኛው አምልኮተ እግዚአብሔር ቀጥሎ ይህ ሁለተኛ አንቀጽ በውስጡ የያዛቸው ፍሬ ነገሮች ማንኛውም ሰው ስመ እግዚአብሔርን በከንቱ ጠርቶ እንዳይቀጣ እንዳይቀሰፍ ሁሉን ቻይ የሆነውን እግዚአብሔርን እንዳላዋቂ ምንም እንደማያይ እንደማይሰማ ቆጥሮ እውነቱን በሐሰት እንዳይለውጥ የእግዚአብሔርን ስም ከስም በላይ መሆኑን እንዲያውቅና እንዲረዳ ያስጠነቅቃል፡፡  ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ስም ከንቱ ያደረገ ሳይቀሰፍ አይቀርምና፡፡  ዘጸ 207፡፡

አንድ ሰው ሥጋዊ ሐብትን ለማትረፍ ሥጋዊ ፍቃድን ለመፈጸም ወይም እውነተኛ ለመምሰል ውሸቱን ሐሰቱን እውነት አስመስሎ ያወራል፡፡  ዮሐ 53-9 በዚህም ጊዜ የፈጣሪውን ስም በከንቱ ይጠራል ማለት ነው፡፡ 

ከሰው ወገን የባልጀራውን ስም ያጠፋ እንደሚፈረድበት በማቴ 522 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡  እንግዲህ ለሰው ስም የሚጠነቀቅ የሰውን መብት የሚጠብቅ እግዚአብሔር ለራሱ ስምማ ምን ያህል ይቀና ይሆንክብሩን ለሌላ እንዳንሰጥ ስሙን በከንቱ እንዳንጠራ ይህ ቃል ያስተምረናል፡፡  በነብዩ አማካኝነት ክብሬን ለሌላ አልሰጥም ብሏልና፡፡  ኢሳ 428፡፡  የእግዚአብሔርም ስም በቀልዱ በቧልቱ በውሸቱም በሐሰቱም መጥራት ክርስቲያናዊ ስነምግባር አይደለምና አንደበታችንን መግታት አለብን፡፡  በዚህም ላይ እንደ መዝሙረኛው ዳዊት አቤቱ ለአፌም ጠባቂ አኑር የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ ብለን መጸለይን የዘወትር ተግባር እናድርግ፡፡  አንድ ሰው ስሙን በከንቱ ሲጠራ ብናገኘው አላዋዊ ከሆነ ማስተማርና ይህን አንቀጽ ጠቅሰን ማስረዳት አለብን፡፡  ግን ሆን ብሎ አድርጎት ከሆነ ማስተባበያ ቃል ልንሰጥበት ይገባል፡፡ 

 

በስሙ ታላቅ ኃይል ያደርጋልና ኢሳ 525-6 ይህን ባናደርግ ግን እኛም በነቀፋ እነዳለንበት ይቆጠራል፡፡  የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ በምስጋና በጸሎት በውዳሴና በዝማሬ ጊዜ ከዚህም ሌላ በበረከት ጊዜ እውነቱን ከሐሰት ባልተለየበት ጊዜ መጥራት ይገባል፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ የክርክር ፍጻሜው በመሐላ ያልቃል ይላል፡፡  ዕብ 616 ስሙን ላከበሩት ምን ያህል በረከትና ክብር እንዳገኙ እንደተደሰቱ ቅዱስ ስሙን በከንቱ የጠሩ የናቁና ያቀለሉ ምን ያህል መርገምና ውርደት እንደደረሰባቸው ከታች ከጥቅሶቹ መሠረት መመልከት ይጠቅማል፡፡  ስለዚህ እንደአምላክነቱ እናመስግነው ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንውረስ፡፡

የአምላክህን ሰነበት አክብር ዘጸ 208-11

ሰንበት ማለት የቃሉ ትርጉም መተው ማቆም ማለት ነው፡፡  እስራኤል ሰባተኛውን ቀን ለእግዚአብሔር የሚቀድሱት እንዲያከብሩት በአስርቱ ቃላት በሦስተኛው አንቀጽ ታዘዋል፡፡  ዘጸ 208-11 እስራኤል ስድስት ቀን ሥጋዊ ስራቸውን እየሰሩ ሰንብተው በሰባተኛው ቀን ግን እረፍት የሚያደርጉበት እለት ነበር፡፡  በዚህ እለት እንኳን ሰው ይቅርና ከእንስሳት ሳይቀር ሰንበትን እንዲያከብሩ ይህ አምላካዊ ቃል /ትእዛዝ/ ያዛል፡፡  ምክንያቱም እግዚአብሔር ከስራው ሁሉ በሰባተኛው ቀን አርፏልና ሰንበትንም ባርኮ ቀድሷታልና፡፡ ዘፍ 22-3

እንግዲህ ይህቺን እለት አምላክ ከሰራው ሁሉ ያረፈባት የቀደሳትና የባረካት እለት ስለሆነች በዚህች የእግዚአብሔር እለት መንፈሳዊና በጎ ስራ ልንሰራባት እንጂ ስጋዊ ወይመ ዓለማዊ ተግባርን ልንፈጽምባት እንደማይገባ ከቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡  ሆሴ 66

በሰንበት ቀን መልካም ሥራ መስራትና መንፈሳዊ ስነምግባር መፈጸም እንደሚገባ ጌታ በቅዱስ ወንጌል በሰንበት ቀን ብዙ በሽተኞችን በመፈወሱ ተቃውሞ ቢደርስበትም ለተቃዋሚዎቹ መልስ ሲሰጥ በሰንበት ቀን መልካም ስራ መስራት ተፈቅዷል ነው ያላቸው፡፡  1212

ከጥንትም ጀምሮ ሰንበት በመባል የምትታወቀው በእብራውያን ዘንድ የምትከበረው እለተ ቅዳሜ ነበረች፡፡  ኤር 1719-27 ከቅዳሜ ይልቅ እሁድ እንድትከበር የሆነበት ምክንያት ጌችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ የተነሳባት ደቀመዛሙርቱም የተገለጠባትና ሰላምን የሰጠባት እለት በመሆኗ ነው፡፡  ዮሐ 2019-22 እንዲሁም በየሳምንቱ እሁድ እየተገለጠ ዘወትር ያጽናናቸው ነበር፡፡  በተነሳ በአምስተኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን የሰጠበት እሁድ ቀን ነው፡፡  ዮሐ 21-4 ከዚህም ቀን ጀምሮ ዋናዋ ሰንበት እሁድ በመሆን ተከበረች፡፡

ደቀመዛሙርቱም በየጊዜው እሁድ እሁድ አንድነት እየተሰበሰቡ አገልግሎታቸውን መንፈሳዊ ተልእኮአቸውን ይፈጽሙበት ነበር፡፡  የሐዋ 207 ምክንያቱም ጌታ አስቀድሞ የሰንበትን ንባብ ከነትርጉሙ አስረድቶአቸዋልና፡፡  ሰንበት ለሰው ልጅ ተፈጠረ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረምና፡፡  ማር 227 በዚህ መልኩ የተቀደሰችውን እለት ለተቀደሰ ተግባር ማዋል ይገባናል፡፡  የቀደሙትን ክርስቲያኖች መምሰል አለብን፡፡  የሐዋ 1129-33 የሰንበት አክብሮት ማለት በሽተኞችን መጠየቅ ችግረኞችን መርዳት የአዘኑትን ማጽናናት መሆን አለበት፡፡  በዚሁም ሁኔታ እለቷም ሰንበት ትባላለች፡፡  እኛም በስም ብቻ ሳይሆን በስራም ክርስቲያኖች እንባላለን፡፡  የሐዋ 244-47 1129-30 ለሥጋ ብቻ አልተፈጠርንም ከመንፈስ የተወለድን መንፈስ ቅዱስም በውስጣችን ያለ የመንፈስ ቅዱስ ልጆች ነንና፡፡  ዮሐ 112-13፡፡  ቲቶ 34-7 ይመልከቱ፡፡  ስለዚህ መንፈሳዊ ስራ መስራት ክርስቲያናዊ ስነምግባር መሆኑን አንዘንጋ፡፡

እናትና አባትህን አክበር ዘዳ 2012

ከእግዚአብሔር በታች ልናከብራቸው የሚገባን ወላጆቻችንን ነው፡፡  በእነሱ አማካኝነት ወደዚህ ዓለም መጥተን ከቁጥር ገብተናል፡፡  ስለዚህ ውለታቸውን በሚገባ ልንመልስላቸው ይገባናል፡፡  ወደ እግዚአብሔር አባትነትም የሚያደርሱን እነሱ መሆናቸውን አንዘንጋ፡፡  ምክንያቱም መክረው አስተምረው አስፈላጊውን እንክብካቤና አስተዳደግ በማድረግ ነው፡፡  ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ የምንችለው ውለታቸውን ጠንቅቀን ያወቅን እንደሆን ነው፡፡  ማንኛውም ሰው ለወላጆቹ መልካም ስራና በጎ ተግባር ሊሰራና ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ 

ያለዚያ ይህንን መልካም ስራና በጎ ተግባር ለሌለው ሰው እንዴት ሊፈጽም ይችላልእግዚአብሔር ሰውን ከሌላው ፍጥረት ለይቶ ስለወደደው እና ስላፈቀረው ከሱ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ በመያዝ እንዲከበር አደረገው፡፡  ሰው ከሌሎች ፍጥረታት የሚለየውና ክብር የሚያሰጠው ወላጆቹን በሚገባ ስለሚያከብርና ስለሚያገለግል ነው፡፡  ስለዚህ የወላጆቹን ትምህርት ተግሳጽና ምክር በደስታ ሊቀበል ይገባዋል፡፡  ማቴ 1918 ኤፌ 61-3 ምሳሌ 18-9 ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ያስተምራል፡፡ 

አትግደል

በእግዚአብሔር መንግስት በአምስተኛው አንቀጽ ሰው በማንኛውም ምክንያት የሰውን ነፍስ እንዳይገድል፣ እንዳያጠፋ አትግደል ሲል ያውጃል፡፡  ህይወትን ለማሳለፍ ስልጣንና ችሎታ ያለው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡  1 ሳሙ 26፡፡  ሰው እንኳን በሌላው ነፍስ ይቅርና በራሱ ነፍስ እንኳን ስልጣን የለውም፡፡  የአባት ነፍስ የእኔ ናት የልጅም ነፍስ የእኔ ናትና ይላል፡፡  ሕዝ 184፡፡  ለሞት ምክንያት የሚሆኑትና የሰው ነፍስ ሊጠፋባቸው የሚችሉ መሳሪያዎች ከዚህ እንደሚከተሉት ተዘርዝረዋል፡፡ 

ቁጣ ብስጭት ዘፍ 4

ቅናት ምቀኝነት ዘፍ 37

የራስን ጥቅም ብቻ በመፈለግ 1 ነገሥት 201-25

በቂም በበቀል 2 ሳሙ 128-29 ከዚህም ሌላ ስካርን አለመጠንቀቅ እብደትን ያጠቃልላል፡፡

በነዚህ የተለያዩ ምክንያቶች የሰው ነፍስ ይጠፋል፡፡  ከእንግዲህ ያለው አጉል ጠባይ የሰው ልጆች እንዲርቁና እንዲጠነቀቁ ይህ ክርስቲያናዊ ስነምግባር አምላካዊ ቃል አትግደል ሲል ያስተምረናል፡፡  እንኳን መግደል ቀርቶ ወንድሙን የተሳደበና ያሳዘነ የገሐነም ፍርድ እንደሚገባው ጌችን በማቴዎስ 521-24 አስተምሮናል፡፡  እንኳን የእግዚአብሔርን ስራ ማበላሸት ቀርቶ አንድ ተራ ሰው የሰራውን ማበላሸት እንዴት ያሳዝናል፡፡  ሰው ለሰው እረዳቱ እንጂ እንቅፋቱ እንዲሆን አይገባውም፡፡  ሰው ለሰው ክብሩ እንጂ ውርደቱ መሆን የለበትም፡፡  ማንኛውም ሰው ያለ ሰው ሊኖር አይችልምና፡፡  ዘፍ 218 አንድ ክርስቲያን ሊገላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡  እነዚህም ምኞትን መተው /መግደል/ ክፉ ፍላጎትን ከልብና ከመንፈሳዊ ህይወት ማራቅና ማሸሽ /መለየት/ ሮሜ 813 ቆላ 35 ይመልከቱ፡፡  በቀል የኔ ነው ስለሚል እግዚአብሔርን መበቀል አይገባንም፡፡  2 ሳሙ 2248 ቂምን በመያዝ ፋንታ ጠላቶቻችንን እንድንወድ ታዘናል፡፡  ሮሜ 1220 ሰው የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ስለሆነ ለቤተመቅደሱ መጠንቀቅ ይገባል፡፡  ማንም ቤተመቅደሱን ቢያፈርስ ይፈርሳልና፡፡  1 ቆሮ 316 ይመልከቱ፡፡

ስለዚህ ይህን አምላካዊ ቃልና ትምህርት በህይወታችን እንስራበት፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ስለዚህ ትእዛዝና ሕግ የሚያስተምረን አለ፡፡  ሰው ከትዕዛዛት አንዱን አፍርሶ የቀሩትን ቢፈጽም ሁሉንም እንዳፈረሰ ይቆጠራል ካለ በኋላ ምክንያቱን ሲያስረዳ አታመንዝር ያለ ጌታ እንዲሁም አትግደል ብሏል፡፡  ባታመነዝርም እንኳ ከገደልክ ሕግን አፍርሰሃል፡፡  ያዕ 28 1-13 በዚህ ቃል መሰረት ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው ሰውን መጥላት ሳይሆን ሰውን መውደድ ሕግን መተላለፍ ሳይሆን ሕግን መፈጸም መግደል ሳይሆን ጠላትን ሳይቀር መውደድና ማፍቀር ምህረት ማድረግ የክርስቲያን ሁሉ ዋና ተግባሩ ሊሆን ይገባል፡፡  ያዕቆብም የሚያስተምረን ይህን ነው፡፡ ጭካኔን ሳይሆን ምህረትን እናድርግ ምክንያቱም ምህረትን ለማያደርግ ምህረት አይደረግለትምና፡፡  ሆኖም ምህረት ፍርድን ያሸንፋል ምህረትን አንለማመድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

አታመንዝር

በእግዚአብሔር ሕገ መንግስት 6ኛው አንቀጽ ክርስቲያናዊ ትምህርታችን ሰው ሁሉ የጋብቻን ሕግ ማፍረስ እንዳይገባው ሲያጠይቅ አታመንዝር ሲል ያውጃል፡፡  አመንዝራ ማለት የራስ ያልሆነውን መፈለግ ነው እንጂ ግዴታ ጾታዊ ግንኙነትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም፡፡  እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት አንድ ወንድ ለአንድ ሴት አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ሰጥቶ መፍጠሩን ጋብቻ ክቡር መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህንንም በአዳምና በሔዋን ተፈጥሮ እንረዳዋለን፡፡  ለአዳም የሚያስፈልገውን እንደሰጠው ዘፍ 224 መመልከቱ ይጠቅማል እግዚአብሔር ጋብቻን ሲመሰርትላቸው እርስ በርሳቸው እንዲረዳዱ እንጂ አንዱ ለአንዱ ሸክም እንዲሆን አይደለም ይህም ዕድል ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ስለሆነ የጋብቻን ክቡርነት ያስረዳናል፡፡  ዕብ 13 የጋብቻ አላማው ልጅ ለመውለድና ዘር ለተመካት ኑሮንም ለማሻሻል ሁሉንም በየድርሻው ፈቃደ እግዚአብሔርን መፈጸም አለበት፡፡  ከዚህ ሌላ በተለያየ ምክንያት ልጅ ላለመውለድ የሚፈልግ ሰው ግን ከተቃራኒ ጾታ መራቅና ለብቻው መኖር አለበት፡፡  ዝሙት ይሆንበታልና፡፡  ዘማዊ ሰው ግን በነፍሱ ከሚቀጣው ቅጣት አስቀድሞ በሥጋው ይቀጣል፡፡  በስንት ወርቅ የማይገኘውን አካሉን ለዘማ ይገብራል፡፡  ኃይሉን ይቀንሳል፡፡  አእምሮውን ያሳንሳል ጤንነቱን በበሽታ ይለውጣል፣ ትእግስቱን ያጣል፡፡  ሰው ተብሎ የሚገመትበትን የክብር ወሰን ያፈርሳል፡፡  በዚህ ዓለም ሊከበር የሚገባው አንዱ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ጋብቻ ነው፡፡  እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ባርኮ ሰጥቶአቸዋልና፡፡  ማቴ 193-6፡፡  ዮሐ 21-11፡፡  የጋብቻ 2 ሕግ ንጽሕና ነው፡፡  ስለዚህ ክርስቲያኖች በንጽሕና ልንመላለስ ይገባናል ምክንያቱም ከዚህ የወጣ የሰይጣን ሕግ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡  የሰይጣንም ስራ የሰውን የድል በር መዝጋት ደረጃውን ማዋረድ ተፈጥሮውን ማርከስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  ሮሜ 124-27፡፡  ዘፍ 194-9 ይመልከቱ፡፡  ብዙ በማግባት ዘር ሊበዛ አይችልም 1 ነገሥት 111-13፡፡  ሆሴዕ 410፡፡  ከዚህ ሌላ ከእግዚአብሔር ርቆ ጣኦት ማምለክ ትእቢተኛ አሉተኛ መሆን በእውነት መንገድ አለመመላለስ አምንዝራ ያሰኛል፡፡  ይህንንም በሚቀጥለው ጥቅስ መመልከት ይጠቅማል፡፡  ኤር 36-10 ሕዝ 231-49 ማቴ 1239 ማርቆስ 838 ይመልከቱ፡፡  እግዚአብሔር ሕጉን ያስተምረን አይነ ልቦናችንን ያብራልን፡፡  በተጨማሪም የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት እንድንርቅ ነው፡፡  1 ተሰሎ 43፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱም ይህን የመሰለ ቃል እናገኛለን፡፡  ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፡፡  በማለት ከጌታ ጋር ሕብረት እንዳላቸው በመግለጽ አሳስቦአቸዋል፡፡  በመቀጠልም ከዝሙት ሽሹ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከስጋው ውጪ ነው፡፡  ዝሙትን የሚሰራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሰራል ይላል፡፡  1 ቆሮ 618-18 ይህ የጳውሎስ ቃል ለእኛም ሕይወት ያስፈልገናል፡፡  ማንኛውም ሰው ኃጢአት በሚሰራበት ጊዜ ከሥጋው ውጪ መሆኑን ተመልክተናል፡፡  ዝሙትን የሚሰራ ሰው ግን ሥጋውን እንደሚበድል እንደሚጎዳ ሐዋርያው ያስተምረናል ከዚህ አይነት ስጋንና ነፍስን ጎጂ ከሆነ ሥራ ሁሉ መራቅ ተገቢያችን ነው፡፡

አትስረቅ ዘጸ 2015

በእግዚአብሔር ሕገ መንግስት በሰባተኛው አንቀጽ በክርስቲያናዊ ስነምግባር ትምህርታችን ማንኛውም ሰው ከራሱ ገንዘብ ንብረት በስተቀር የሌላውን ሰው ገንዘብ ንብረት እንዳያባክን እንዳይቀንስ እንዳይነካ አትስረቅ ሲል ያውጃል፡፡  ሌላው የደከመበትን ገንዘብ ሐብት ንብረት መቀነስ አካሉን እንደማጉደል ነውና ምክንያቱም ሐብት ገንዘብ የሕይወት ምንጭ የደምስር ነውና፡፡  የስርቆት ምክንያቱ ስልቱ ብዙ ነው፡፡  ግና ስርቆት ይባላል፡፡

1. በግልጽ በማስፈራራት በማስገደድ በሐይል የሚወስዱት ስርቆት ይባላል ግን ይህ አየነቱ ንጥቂያ፣ ቅሚያ፣ ዝርፊያ፣ ውንብድና ይባላል፡፡  ሰው የሚወጣበትን የሚገባበትን ቦታና ጊዜ ጠብቀውና አጥንተው ይህን ስራ አድርገው ሲዘርፉ ሲነጥቁና ሲቀሙ ይኖራሉ፡፡  ስለዚህ አትስረቅ ያለውን ሕግ አፈረሱ ማለት ነው፡፡  ሉቃ 1030

2. ጨለማን ተገን አድርገው በስውር የሚሰርቁ አሉ፡፡  ይህም አይነት ስርቆት ንቃት፣ ትጋት፣ ቅልጥፍና የኑሮ ዘዴ መስሎአቸው እንደ ታላቅ ስራ ይቆጥሩታል፡፡  ሌላው አቅቶት የተወው ለእነሱ ብቻ የተሳካላቸው ይመስላቸዋል፡፡  ወንጀል መሆኑንም አያውቁትም፡፡

3. ማታለል፣ ማጭበርበር፣ ስፍር ማጉደል ሚዛን ማቅለል ነው፡፡  ይህመ ስርቆት መሆኑን ማንም ሳያውቀው እንደ ኃጢአትም ሳይቆጠር ገዢውም ሆነ ሻጩ የሚፈጽሙት ወንጀል ነው፡፡  ገበያ ወጥቶ ይህን የማይፈጽም ማንም የለም፡፡  ግን ይህን ሰራሁ ብሎ ንስሐ የገባ የለም፡፡

4. ጉቦ መቀበል ነው፡፡  ይህም ታማኝነትን ማጉደል ሕዝቡ ይሰራልና ያገለግለናል በማለት መርጦት ሳለ ሕዝቡን ሲያታልል ገንዘቡን ሲበዘብዝ መገኘት ምን ያህል አሳዛኝ ነው፡፡

5. በምትሐት ያልያዙትን እንደያዙ አስመስለው የሚሰርቁትና የሚቀሙት ነው፡፡  የሰውን ንብረት ለመውሰድ የሚደረግ ዘዴ ስለሆነ ስርቆት ይባላል፡፡  ይህ ሁሉ የስርቆት ስልት ያታላይነት ስራ መሆኑን እያወቀ ይሰርቃል ያታልላል፡፡  በዚህም ሁኔታ እንዳለ አቅሙን ሳያውቅና ንስሐ ሳይገባ ከነኃጢአቱ በዚህ ዓለም ይኖራል ብዙ ትርፍ የሚገኘው በመስረቅ በማጭበርበር ይመስለዋል፡፡  ግን ያለውን በተወሰነ ዋጋ ቢሸጥ ቢለውጥ ኃጢአት ሳይሰራ ንግዱም ሳይቀር ሁለት አይነት ትርፍ አተረፈ ማለት ነው፡፡  ሌላው የአፍ ሌባ ነው፡፡  ምሥጢር የሚሰርቅ በድብቅ የሚቀረውን ነገር እንደ መርዶ ነጋሪ የሰማውን በቶሎ ለማውራት የሚቸኩል ማንኛውም በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፡፡  ስርቆት ጸያፍ ነው፡፡  የሁላችንም ጥብቅ እርምጃ ፍቅር ሰውን ለመጥቀም ይሁን እንጂ ሰውን የሚጎዳ እነዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡  ለስራ እንሰለፍ ለስራ ዘወትር የነቃን እንሁን እራሱ እግዚአብሔር ሰራተኛ ነውና፡፡  ያለውን ሁሉ ሰርቶ እንጂ ከማንም ቀምቶ ለራሱ አላደረገም፡፡  ታማኝነትን እናሳይ የክርስቲያን ስራ ይህ ነውና፡፡

በሐሰት አትመስክር ዘጸ 2016

የክርስቲያናዊ ስነምግባር 8ኛው አንቀጽ ማንኛውም ሰው በሐሰት መመስከር እንዳይገባው በባለንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር ሲል ያውጃል፡፡  በሐሰት መመስከር ማለት ጥቅም የሚገኝበት መስሎት እውነቱን ነገር በሐሰት ለውጦ ሐሰትን መናገርና በአደባባይ በሐሰት መማል ነው ወይም ወዳጁን የጠቀመና ጠላቱን የጎዳ መስሎት የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ሐሰት ይናገራል፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሐሰት መሆኑን ያውቃል፡፡  ስለዚህ ሆን ብሎ ይሰራዋልና በአንድ ጊዜ ሁለቱንም ሕግ አፈረሰ፡፡  ከእውነት የወጣው ሁሉ የሰይጣን የግብር ልጁ ነው፡፡  ሰይጣን እራሱ የሐሰት አባት ነውና፡፡

ዮሐ 844 ሰው በሚናገረውም ሆነ በሚሰራው እግዚአብሔርን ምስክር ማድረግ ይገባዋል፡፡  እውነትንም መለማመድና ማዘውተር ይኖርበታል፡፡  ሐሰት ከሆነ ሐሰት እውነት ከሆነ እውነት እንድንል በቅዱስ ወንጌል ታዘናል፡፡  ማቴ 537 የሰው ልጅ መርዝነቱን ሳያውቅ የተጎዳበት ሐሰት ነው፡፡  ዘፍ 34-5 የሚያስደንቀው ነገር የሰው ልጅ እባብ ሲያይ ይሸሻል፡፡  ሐሰትን ሲናገር ግን ወደ ኋላ አየልም፡፡  መርዙ እኔንም ሆነ ሌላውን ይጎዳል ብሎ አያስብም፡፡  ክርስቲያን የሆነ ሰው ግን ከእንዲህ አይነቱ የሰይጣን ስራ እጁን ማስገባት የለበትም፡፡  በአፉም ሐሰት አይናገርም በቃሉም ውሸት አይናገርም አይገኝም፡፡ 

የባልንጀራህን ሐብት አትመኝ

በእግዚአብሔር ሕገ መንግስት በክርስቲያናዊ ስነምግባር ትምህርታቸን በዘጠነኛው አንቀጽ ማንኛውም ሰው ከሐብቱ በቀር ሌላ እንዳይመኝ የባለንጀራህን ሐብት ቤት አትመኝ በማለት ያስተምረናል፡፡  ምክንያቱም መጥፎ ሐሳብ መጥፎ ስሜት ወደ ማድረጉ ያመራናልና፡፡  አንድ መጥፎ ስሜት ያለው ሰው ወዲያውኑ ከልቡ ካልጣለው ከዋለ ከአደረ ዘንድ በሥራ በድርጊት መገለጡ አይቀርም፡፡  ከስራውም ዘንድ ሕግ አፍራሽ ይባላል፡፡  ኃጢአት በሦስት አይነት መንገድ ይሰራል

በማሰብ

በማየትና በመናገር

በመስራትና በማድረግ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ሐሳብ የኃጢአት ሁሉ መሰረት ነው ማለት ነው፡፡  ሐሳብ ሲመጣ ሲፈጠር ሊመነጭ የሚችለው ስራ ከመፍታት ዋዛ ፈዛዛ ቀልድ በማብዛት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡  ስለዚህ ሐሳብ የኃጢአት ሥርና መሰረት ስለሆነ የመጥፎ ነገር የክፋት ምንጭ መሆኑ ከታወቀ በዚህ አይነት ሐሳብ እንዳንጠመድ ሥራን ማዘውተር ይኖርብናል፡፡  አንድ ሰው መጥፎ ሐሳብ ሲመጣበት ወዲያውኑ ስመ እግዚአብሔርን መጥራትና ገጹን በመስቀል አምሳል ማማተብ አለበት፡፡  ሁለተኛ እንዳያስበው ካላደረገ ኃጢአት አይሆንበትም፡፡  በልቡ አላዋለውም አላደረገውምና፡፡  ከልብ የተረፈውን አፍ ይናገራል እንደተባለው፡፡  ቀንና ሰአት ሳይለይ በየጊዜው የሚአስበውና የሚአሰላስለው ለመስራት ኃይልና ጊዜ አጥቶለት ነው እንጂ የቆየ እንደሆነ ምንም ሳይሰራው ኃጢአት ይሆንበታል፡፡  የሰው ልብ ዘወትር ከሐሳብ የማይለይ ስለሆነ ደጉን መልካሙን ጥሩ ጥሩ የሆነውን ነገር መመኘትና ማሰብ ይገባናል፡፡  እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ነገር እንዲገልጽልን እንደ ዳዊት አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ ብለን ልንጸልይ ይገባናል፡፡

ባልንጀራህን እንደ እራስህ አድርገህ ውደድ ዘሌዋውያን 1916-18

በዚህ የሕግ ሁሉ ማሰሪያና መደምደሚያ በሆነው ክርስቲያናዊ ስነምግባር ትምህርታችን በአሥረኛውም አንቀጽ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፡፡  ባለእንጀራ ሲባል በቅርብ የሚታወቅ ብቻ አይደለም፡፡  በተፈጥሮ የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ ለሰው ልጅ ወንድም ባለንጀራ ነው እንጂ እንደራስህ አድርገህ የሚለው አንድ ሰው ለራሱ ክብር ለራሱ ኑሮ መሻሻል ለራሱ ሕይወት ጤንነት የሚጠነቀቀውን ያህል ለባለንጀራውም ሊጠነቀቅና እንደራሱ ሊወደው ይገባል፡፡  ማቴ 712 በዚህ ሁኔታ ባለንጀራችን እንደራሳችን እንድንወድ ይህ ቃል ያሳስበናል፡፡  እግዚአብሔርን ለመውደዳችን መለኪያ ሚዛኑ ይህ ነውና፡፡  1 ዮሐ 521፡፡  የመጀመሪያው አምላካዊ ሕግና ይህ የመጨረሻው ክርስቲያናዊ ስነምግባር መጀመሪያና መጨረሻ ስለሆነ ኦሪትም ነብያትም በነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት እንደተሰቀሉ ጌታ ያስተምረናል፡፡  ማቴ 2236-40፡፡  በሰው ላይ ፍርሐት ይሉኝታ የሚያሳድረው ፍቅር ነው፡፡ በሰው ሕሊና ሰላም የሚቀረጸው ከፍቅር የተነሳ ነው፡፡  አንዱ ለአንዱ የሚያስብለትና ሊረዳው የሚችል ከፍቅር የተነሳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  ፍቅር ለሰው ልጅ ሰው ለመሆኑ መታወቂያው ፍቅር ነው፡፡  በተለይ ለክርስቲያኖች ሁሉ ምልክቻው ፍቅር መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡  ክርስቶስ ፍቅርን ለተከታዮቹ ልዩ ምልክት አድርጎ ሰጣቸው፡፡  የእኔ መሆናችሁን ዓለም የሚያውቀው በፍቅሬ ስትኖሩ ነው ብሎ የፍቅርን ከፍተኛነትና ታላቅነት አስረድቶአቸዋል፡፡

ፍቅር በሰው ልጅ ላይ የሚሰነዘረውን የበደል ፍላጻ የምትከላከል አጥር ናት፡፡  ፍቅር ከአለ ጠላት የለም፡፡

ፍቅር ካለ እድሜ ይረዝማል፣ ሁሉን ይወዳል፣ ሁሉን ያፈቅራል፣ ሁሉን ያከብራል፡፡  ፍቅር ከሌለህ ግን የአገኘህ ሁሉ ሊያጠፋህ ይፈልጋል፡፡  ምቹም ጊዜ ይመርጣል፡፡  ወንድሜ ወንድሜ እህቴ እህቴ መባባልን ተማር በዚህም ሕግጋትን ሁሉ ትፈጽማለህና፡፡  ፍቅር የስነምግባር ትምህርታችን ማሰሪያ መጀመሪያና መጨረሻ ስለሆነ በፍቅር ጎዳና መመላለስ ይገባናል፡፡  በዚህም ትእዛዛትን ሁሉ እንፈጽማለን፡፡ 

ስድስቱ ቃላተ ወንጌል

በዚህ ርእስ ውስጥ የምናገኛቸው 6 የወንጌል ቃላት ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ የተናገራቸው ለሕዝብ ያስተማራቸውና ቀደም ብሎ በዘመነ ኦሪት ለሙሴ የተሰጡትን ሕጎች ፍጹማን ያደረገባቸው ናቸው፡፡  ስለነዚህ አምላካውያን ሕጎችና ፍጹማንም ስለሆኑ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ይባላሉ፡፡  ምክንያቱም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሊማራቸውና ሊአስተምራቸው ስለሚገባ ነው፡፡

አንቀጽ 1

በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል ማቴ 522

ወንድም ሲባል በስጋ ብቻ የሚዛመድ ሳይሆን በነገድ፣ በቤተሰብ በሐገር በቃልኪዳን በመንፈስ ቅዱስ በሃይማኖት በስራ በመረዳዳት እና በመሳሰለው ሁሉ ወንድም ይባላል፡፡  ቁጣ ሲልም በሚገባና በማይገባ አንዱ በአንዱ ላይ ተነስቶ የሚናገረውና የሚፈርደው ነው፡፡  ቁጣ ወደ መግደል ከሚያደርሱ ነገሮች አንዱ ነው፡፡  ዘፍ 2744-45፡፡  ኃጢአት የሌለበት ተገቢ ቁጣ በማቴ 35 በኤፌ 426 እንመለከታለን፡፡  ከቅናትና ከቂም የመነጨ ቁጣ ሰይጣናዊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  ዘፍ 4741 ይመልከቱ፡፡  ሳኦል በዚህ አይነት ቁጣ ዘወትር ይቆጣ ነበር፡፡  1 ሳሙ 2030-34 ያንብቡ፡፡  በዚህ ሁኔታ የሚቆጣ ሰው ጠብን ያነሳሳል፡፡  ምሳሌ 158፡፡  ክርስቲያን ግን ከዚህ መሰል ቁጣ መራቅ ይኖርበታል፡፡  ሮሜ 1219፡፡  ክርስቲያን ሊያስወግዳቸው እና ከነሱም ሊሸሽ ሊርቅ የሚገባው በኤፌ 431 በቆላ 38 ያዕ 119-21 ያሉትን ነው፡፡  በለዘብተኛ ምላስ የሌላውን ሰው ቁጣ ማብረድ እንደሚቻል በምሳሌ 151-4 እንማራለን፡፡

 አንቀጽ 2

ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ አመነዘረ

ማመንዘር ማለት ሰው ከትዳር ጓደኛው ሌላ ቢወድና ቢለምድ አመነዘረ ይባላል፡፡  ጌታ ግን ማንም ሰው በዝሙት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ አርቆ አጥሯል፡፡  ሰው በተግባር የሚፈጽመውን በልቡ ያሰበውን ስለሆነ በልቡም እንዳመነዘረ ይህ ቃል ያስተምረናል፡፡  በዚህ ቃል መሰረት የዝሙት የምንዝር ማሰሪያ የሆኑትን ሁሉ ማስወገድ ይገባናል፡፡  ማቴ 529፡፡  ማቴ 188፡፡  ማር 943-58፡፡  ምሳሌ 625፡፡  የጌታ አባባል ሴትና ወንድ ሳይተያዩ ይኑሩ ማለት ሳይሆን በዝሙት መንፈስ አተኩሮ የሚመለከት አይኑር፡፡  አንዱ የሌላውን አይመኝ ማለቱ ነው፡፡

ዝሙት በብዙ አቅጣጫ ይታወቃል፡፡  በዘፈን ሮሜ 1313 በውዝዋዜ በእንቅስቃሴ ማር 621 በዘመናዊ ሙዚቃ ገላ 519-21 በዓለማዊ ዳንስ /ዳንኪራ/ በነዚህና በመሳሰሉት ነው፡፡  ይህን ሁሉ የዝሙት ሐሳብ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ያውቃል፡፡  ሕዝ 115 ኤር 1710 ስለዚህ የልብን ምንዝርነት ማስወገድ ይገባል፡፡  እግዚአብሔር በነብዩ ኤርሚያስ አድሮ የሚያስተምረን እያንዳንዳችን በሰራነው መጠን ዋጋችንን እንደሚከፍለን ነው፡፡  ይህን የመሰለ ቃል በመዝ 6112 እና በራ 2212 እናገኛለን፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን በአገልጋዮቹ አማካኝነት ያስተማረንን ትምህርት ያስተላለፈልንን መልዕክት ሰምተን በስራ ላይ ማዋል ይገባናል፡፡  ዋጋችንን የምንቀበለው በሰራነው መጠን ነውና፡፡  1 ቆሮ 314፡፡

አንቀጽ 3

ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል የተፈታችውንም የሚገባ ያመነዝራል ማቴ 531-32

ዝሙት ቀደም ብለን በአንቀጽ 2 የተመለከትነውን ይመስላል፡፡  ይሁን እንጂ ከጋብቻ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ስጋዊ ግንኙነት ሁሉ ዝሙት ይባላል፡፡  ይህም በክርስቲያኖች ዘንድ የተከለከለ ነው፡፡ 1 ቆሮ 69-18 በሌላ መልኩ ዝሙት እውነተኛ የሆነውን ያልሆነውን አምልኮ ይገልጣል፡፡  ማር 838 እንመልከት፡፡  በዝሙት ምክንያት እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለየውም ይላል ማቴ 196፡፡  ጋብቻ ሕጋዊና ምስጢራዊ በአምላክ የተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ሰው ሁሉ ጋብቻውን አክብሮ መያዝ ይኖርበታል፡፡  ዘፍ 221-24፡፡  ሙሴም በሆነው ምክንያት ሁሉ ሰው ሚስቱን የፍቺዋን ጽሕፈት ሰጥቶ እንዲፈታ አዞ ነበር፡፡  ዘዳ 241፡፡  ጌታ ግን ሙሴ ይህን ያለበት ምክንያት በማብራራት መልስ ሰጥቶበታል ማቴ 19 አንብብ፡፡  የክርስቲያን ጋብቻ ግን እንዲህ አይነት ሳይሆን በስጋውና በደሙ ማህተምነት የታተመ በመሆኑ ምስጢራዊ ጋብቻ ይባላል፡፡  2 ቆሮ 112፡፡  ኤፌ 521-33፡፡  ጋብቻ ክቡርና መኝታውም የተቀደሰ ነው፡፡  ዕብ 134፡፡  ስለዚህ ጋብቻን አክብረው፡፡

አንቀጽ 4

እኔ ግን እላችኋለሁ ከቶ አትማሉ ማቴ 534-37

መሐላ ሰው ቃሉን እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ የእግዚአብሔርን ስም ወይም ሌላ ነገር ይጠራል፡፡  ይኸውም እውነት እንዲሆንለት ነው፡፡  ዘፍ 2123 ተመልከት፡፡  በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን አንዳንድ የእግዚአብሔር ሰዎች እውነትን ከሐሰት ለመለየት እና በእውነት ለመመስከር ሲሉ ስመ እግዚአብሔር ጠርተው ይምሉ ነበር፡፡  1 ነገ 1815፡፡  መሐላ የነገር ሁሉ ማሰሪያ መደምደሚያ ነው፡፡  ዕብ 616፡፡  ሰሎሞን ማንም ሰው በጌታ መቅደስ ቢምል እግዚአብሔር በዳኝነት እንዲፈርድ በጸሎቱ እግዚአብሔርን ጠይቋል፡፡  1 ነገ 831-33፡፡  ከዚህ በተረፈ ነገራችን ሁሉ እውነት ከሆነ እውነት ሐሰት ከሆነ ሐሰት መሆኑን እንድንናገር ጌታ አስተምሮናል፡፡  37 ጌታ አትማሉ ያለበትን ምክንያት በማያስፈልገው ነገርና በሐሰት አትማሉ ማለቱ ነው፡፡  ሐዋርያው ያዕቆብም ይህን የመሰለ ቃል ጽፎልናል፡፡  ያዕ 512፡፡  ማቴ 538-48

አንቀጽ 5

ባለንጀራህን ክፉውን በክፉ አትቃወሙ

ክርስቲያናዊ ስነምግባር የሚያተኩረው በሰዎች ላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  ክፉ ሲል ሰውን እንጂ ሌላ አያመለክትም፡፡  ሰይጣንም ክፉ ተብሏል፡፡ ሰይጣንን ግን እንድንቃወመው ታዘናል፡፡  ማቴ 537፡፡  ያዕ 47፡፡  ክፉን በክፉ የምንቃወም ከሆነ ሰይጣንን አልተቃወምነውም ማለት ነው፡፡  ክፉውን በመልካም ስናሸንፍ ግን ሰይጣንን መቃወማችን መሆኑን እንወቅ፡፡  ሮሜ 1221፡፡  ይህን ትእዛዝ የምንፈጽመው ብርቱዎች ስንሆን ደካሞች ጥበበኞች ስንሆን ሞኞች በመሆን ነው፡፡  1 ቆሮ 410-13፡፡  እንግዲህ ክርስቲያን ክርስቶስን መምሰል ይገባዋል፡፡  እሱ ሲቃወሙት አልተቃወመምና፣ ሲሰድቡት አልተሳደበምና፡፡ ማቴ 2712-14፡፡  1 ጴጥ 223 ተመልከት፡፡  ክርስቲያኖች ለክፉዎች ሊጸልዩላቸው ይገባል፡፡  የሐዋ 757-60፡፡

አንቀጽ 6

በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሙአችሁን መርቁ ማቴ 543-48

በዚህ በስድስቱም ቃላት መደምደሚያ ፍቅረ ቢጽን አፍቅሮ ጸላዕትን እንማራለን፡፡  በብሉይ ኪዳን ጠላትህን ጥላ ባለንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚል ነበር ግን ጠላታችሁን ውደዱ ክፉውን በክፉ አትቃወሙ ሲል ያስተምረናል፡፡  በዚህም አባባሉ ጠላትህን ጥላ የሚለውን ቃል ሽሮታል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን ጠላቶቻችንን መውደድ ክርስቲያናዊ ስነምግባር ስለሆነ ልንፈጽመው ይገባናል፡፡  እርሱ የወደደን ገና ጠላቶቹ ሳለን ነውና፡፡  ሮሜ 58፡፡  ይህን ቃል ሐዋርያው ለቆላስይስ ሰዎች ደግሞ ጽፎላቸዋል፡፡  ቆላ 121-2፡፡  እግዚአብሔር ሁሉን ይወዳል የሚፈልጉትንም ይሰጣቸዋል፡፡

ማቴ 544-46፡፡  እኛም እንደሰማያዊው አባታችን ሁሉን አስተካክለን እንውደድ፡፡  ጠላታችን ቢራብ እናብላው ቢጠማም እናጠጣው ሮሜ 1220፡፡ ስለዚህ መልካም እናድርግላቸው እንጂ ክፉውን በክፉ እንድንቃወም ክርስቲያንነታችን የሚለካው ይህን አምላካዊ ቃል /ትምህርት/ ስንፈጽም ነውና፡፡ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

መደቦቻችን

No events

የመፅሓፍ ቅዱስ ጥቅስ

readings "  በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፥ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና"   

              2ኛ ወደ ተሰሎን 2:13

በኣባ ሳሙኤል የቀረቡ መፃህፍትና ቪቺዲዎች

abb 1

ካባቶኣንደበት

stanthony"ለእግዚኣብሄር ከወንድምህ በላይ ውደደው ለወንድምህ ደሞ ከነፍስህ በላይ ውደደው"   ኣባ ይስሓቕ ሶርያዊ

ካባቶች ምክር

stanthony"ኣንዲት የክፋት ቃል ለመልካም ሰው ክፉ ታደርገዋለች፥ ኣንዲት መልካም ቃል ግን ለ ክፉ ሰው መልካም ታደርገዋለች።"    ኣባ መቃርዮስ 

saying fathers

stanthony"If then we have angels, let us be sober, as though we were in the presence of tutors; for there is a demon present also."   John Chryssostom

saying of fathers

stanthony"Let books be your dining table, / And you shall be full of delights. / Let them be your mattress,/And you shall sleep restful nights"   Ephraim the Syrian

 

              በነዚ ላይ በመጫን ይከተሉን

  twitter-logo-circular-OFFfacebThis email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

adress